Description
ከምዕራባዉያን ፈላስፎች ታላቅ ክብር የሚቸረው ባዉሴት እግዚአብሄርን ቢያገኘው፤ እግዚአብሄርም አንድ ጥያቄ ብቻ የማቅረብ እድል ቢሰጠው ያ ጥያቄ ምን ሊሆን እንደሚችል በተማሪዎቹ ተጠይቆ ሲመልስ ፦ “ሄዋንን እንዴት እንደፈጠርካት ንገረኝ እለው ነበር” አላቸው። ባዉሴት ይህን ይበል እንጂ በሌላ አጋጣሚ ሲናገር፦ “እግዚአብሄር አዳምን ፈጥሮ ከጨረሰ በኋላ አተኩሮ ተመለከተዉና ከዚህ የተሻለ መስራት እችል ነበር በማለት አሰበ። ለጥቂት ጊዜም አሰላሰለና ወንድን በመፍጠሩ ተጸጸተ” ይለናል። እግዚአብሄር ሄዋንን ስለመፍጠሩም ቢሆን ባውሴት “እጠራጠራለሁ” ብሏል። "ለዚህም ነው እግዚአብሄር ከአዳም በኋላ እምብዛም ሰው ለመፍጠር ያልተጨነቀው" ይላል።
“እግዚአብሔር ሔዋንን የፈጠረበት ብቸኛው ምክንያት የአዳም ጥያቄ ነው” የሚሉን ምዕራባዉያን ፈላስፎች ደግሞ “ለነግሩ ሄዋን ሳትፈጠር አስቀድሞ ብዙ ተባዙ ስላለን ምድርን ለመሙላት የእሷ መምጣት አስፈላጊ አልነበረም። የሚገርመው ግን ከጎኑ አጥንት ወጥታ ተመልሳ የአዳም የጎን ዉጋት መሆንዋ ነው” ይላሉ። ፈላስፎቹ አክለዉም፦ “እግዚአብሔር በመጀመሪያ ዓለምን ፈጠረ። በቀጣዩ ቀን ሰዉን ፈጠረና ከስራው ሁሉ ዓረፈ። በማግስቱ ሴትን ፈጠረ። ከዚያ ቀን ጀምሮ እግዚአብሔርም ሆነ ሰው እረፍት አላገኙም” ይለናል።
ሄዋንም እግዚአብሔርን መጠራጠሯ ደግሞ አልቀረም። በተለይም አዳም በገነት ዉስጥ ሲዞር አምሽቶ ከመጣ ቁጣዋና ግልምጫዋ አዳምን ማበሳጨት ጀምሮ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን አዳም ሲዞር ካመሸበት በድካም ተመልሶ አልጋው ላይ ጎኑን እንዳሳረፈ እንቅልፍ ይዞት ሄዷል። ከእንቅልፉ በድንገት የባነነው ሔዋን ደረቱን ስትቆነጥጠው ነበር፤ በድንጋጤ የነቃው አዳም ምን እያደረገች እንደሆነ ሔዋንን ጠየቃት። የሔዋን መልስ አጭር ነበር፦ “የጎድን አጥንትህን እየቆጠርኩ!” (እግዚአብሔር ሌላ ሴት ሰርቶለት ይሆናል ብላ መጠርጠሯ ነበር።)
አንድ በምዕራባዉያን ዘንድ የተለመደ ቀልድ ላዉጋችሁ። በምድር ላይ የነበረው የሰው ዘር በሙሉ ይሞትና ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይሄዳሉ። ታዲያ በዚያ እግዚአብሔር ለሁሉም አንድ ትዕዛዝ ይሰጣል። ይኸዉም ወንድን የበደሉ ሴቶች በግራ በኩል እንዲሰለፉና እንዲመዘገቡ ነበር። ሴቶች በሙሉ ይሰለፉና ይመዘገባሉ። ምዝገባው ሲይልቅ በሉ ወደ ገነት ሂዱ ይላቸዋል። የወንዶች ተራ ይደርስና በሴት የተበደላችሁ ወንዶች በአንድ መስመር፤ ሴትን የበደላችሁ ደግሞ በሌላው መስመር ተሰለፉና ተመዝገቡ ይላል። በሴት የተበደሉት ሰልፍ በወንዶች ሲሞላ ሴትን በበደሉት ሰልፍ ላይ የቆመው ግን አንድ ወንድ ብቻ ነበር። እግዚአብሔር ሰልፉን ሲመለከት በጣም ተቆጣና፦ “እናንተ በእኔ መልክና ምሳሌ ሰርቻችሁ በሴት ስትበደሉ መኖራችሁ ሊያሳፍራችሁ ይገባል። በእሱ ደስ የሚለኝ አንዱ ልጄን ተመልከቱት፤ ከእሱም ተማሩ። ልጄ ሆይ በአንተ ኮራሁ። እንዴት በዚህ ሰልፍ እንደገባህ በል ለሌሎቹ ንገራቸው” በማለት እግዚአብሔር አዘዘው።
ሰዉዬው ግን ግራ በተጋባ መንፈስ፦ “ጌታ ሆይ! በዚህ በኩል ለብቻዬ መቆሜ ለእኔም ግራ የገባኝ ነገር ነው። ምክንያቱም በዚህ በኩል እንድሰለፍ ያዘዘችኝ ሚስቴ ነበረች” በማለት መለሰለት።
ምንጭ፦
ጥበብ መጽሃፍ
ቅጽ 1
9ኛ እትም
ከጲላጦስ
(ኃይለጊዮርጊስ ማሞ)
ገጽ 251 – 253
መጽሐፉን በመግዛት ሙሉ ታሪኩን ማንበብ ትችላላችሁ
Bin Yam
ምርጥና አስተማሪ የፍልስፍና ጽሁፍ – መጽሐፉን በመግዛት ሙሉ ታሪኩን እንድታነቡት ጋበዝኳችሁ።