ወደ ሴቶች ትሄዳለህን? እንግዲያዉስ ጅራፍህን ዘንግተህ አትሂድ

Popular
4.52 reviews
4.50

Report Abuse

Description

“ዛራቱስትራ ሆይ! ራስህን ከዓለም አርቀህ በደመናው ዉስጥ ለምን ትዳክራለህ? እሱ ቢያቅትህ ደግሞ በራስህ መጎናጸፊያ ፊትህን ሸፍነህ ለመደበቅ ሞክረሃል። ለመሆኑ ይህ የተሰጠህ ‘ጸጋ’ መሆኑ ነው? ወይንስ ስትወለድም ለዚሁ ታቅደህ የተፈጠርህ ነህ? ወይስ የሌቦች ወዳጅና የዲያብሎስ ጓደኛ መሆንህን ለማሳየት ነው?”

እንዲህ አይነቶቹ ጥያቄዎች በብዛት ከሴቶች ይወረወሩልኛል። አንዳንዴ የኔ ምላሽ እንዲህ ይሆናል፦ “እዉነት እላችኋለሁ! ወደምድር ስመጣ የተሰጠኝ ሃብት ቢኖር በዉስጤ ያለችው ጥቂት እዉነት ነች… ዳሩ ይህች ሃብቴ ጉርምስናውን እንደጀመረ ወጣት ሃያል ነበረች፤ አፏን አጥብቄ ባልይዘዉማ ኖሮ ጩኸቷ እጂግ ሃያል በሆነ ነበር…”

እንዲህና እንዲያ እየመለስኩ በመንገዴ ስጓዝ የጸሃይ መጥለቂያ በደረሰበት ሰዓት አንዲት አሮጊት በጎዳናው ላይ ወደ እኔ ስትመጣ ተመለከትኩ። አጠገቤ ደርሳ የምትለኝን ለመስማት ጆሮዎቼን ከፈትኩ፤ እሷ ግን ለነፍሴ ተናገረቻት፦

“ዛራቱስትራ ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ ሲናገር አደመጥኩ፤ ለመሆኑ ስለሴቶች የሚናግረዉስ የለዉም?”

እኔም፦ “አንድ ሰው ስለወንዶች ብቻ ከተናገረ እግረ መንገዱን የሴቶችን ጉዳይ እንዳነሳ ይቆጠራል” በማለት መለስኩላት።

“የለም! ዛሬ ስለሴቶች ትናገር ዘንድ እለምንሃለሁ። የቱንም ያህል ስለሴቶች መጥፎ ነገር ብትናገር እንኳን እድሜዬ የገፋ አሮጊት በመሆኔ መሽቶ ሲነጋ እንደማላስታዉስብህ በእርግጠኝነት እነግርሃለሁ…” በማለት አስጨንቃ ያዘችኝ

እኔም የአሮጊቷን ጥያቄ መመለስ ግዴታዬ መስሎ ስለተሰማኝ ስለሴቶች እነግራት ዘንድ ጀመርሁ፦

ሴት ልጅ ሁሉ ነገሯ እንቆቅልሽ ነው፤ በሴት ልጅ ዉስጥ ላለው እንቆቅልሽ ደግሞ መልሱ አንድ ነገር ብቻ ነው… እርግዝና። ወንድ በሴት የሚፈለግበት ዓላማ አንድ ብቻ ሲሆን እሱም ልጅ መስጠት ነው። ሴት ግን ለወንድ ምን ታደርግለታለች?

“እዉነተኛ ወንድ በህይወቱ ዉስጥ የሚፈልገው ሁለት ነገር ብቻ ነዉ - አደጋ እና ለዉጥ። ስለዚህም ሴትን እንደ አደገኛ መጫወቻው ይከተላታል። ወንድ ለጦርነት እንደሚሰለጥነው ሁሉ ሴት ደግሞ ጀግኖችን ደጋግማ በመፍጠር ትሰለጥናለች - የቀረዉማ መግለጫዋ ክፋት ነው።

“ጣፋጭ ፍሬዎች በጀግና ሰው ጣእም የተወደዱ እንዳልሆኑት ሁሉ ሴት ደግሞ በአንጻሩ እጅግ ተወዳጅ ሆናለች። ምነው ቢባል ከጣፋጭ ፍሬ ይልቅ የሴቷ መራርነት በወንዱ ዘንድ እጂግ የተወደደ ነውና።

“ከወንዱ ይልቅ ሴቷ ህጻናትን በሚገባ የመረዳት ስጦታ አላት፤  ነገር ግን ወንዱ ከህጻናቱ ሁሉ የባሰ ህጻን ሆኖ ሳለ ሴቷ ግን አትረዳዉም…

“በእዉነተኛ ወንድ ዉስጥ እኮ የተደበቀ ህጻን አለ፤ እለት እለትም አፈትልኮ በመዉጣት መጫወትን ይሻል። ሴቶች ሆይ! በወንድ ዉስጥ የተደበቀዉን ይሄን ህጻን ፈልጋችሁ አግኙት!

“ሴቶችም እንደከበረ ድንጋይ ዉድ ሆኑ፤ በፍቅራችሁ ላይ የኮከብ ነጸብራቅ ይረፍበት! ተስፋችሁም ‘ታላቁን ሰው አረግዛለሁ!’ የሚል ይሁን…

“በፍቅራችሁ ዉስጥ ጀግንነት ይኑር! በፍቅራችሁ ዉስጥ ፍርሃትን የሚጭረዉንም ለከፋ ቅጣት ዳርጉት… በፍቅራችሁ ዉስጥ ክብራችሁን የምትሸምቱ ሁኑ። እርግጥ ነው ሴት ልጅ ስለክብር ያላት እዉቀት እጂግ ዝቅተኛ ነው፤ ቢሆንም ቢያንስ ፍቅራችሁ ክብራችሁ ይሁን! ሁልጊዜም ከምትፈቀሩት በላይ አፍቅሩ! በማፍቀርም ማንም እንዳያሸንፋችሁ በርቱ!

“ወንዱ ሴቷ ስታፈቅረው ሊራራለት ይገባል፤ ምክንያቱም በፍቅሯ ዉስጥ ያለው መስዎእትነቷ ሃያልና ከፍቅሯ በቀር ሁሉን ነገር ከንቱ አድርጋ የምትመለከት በመሆኗ ነው…

“እንዲሁም ሴቷ ስትጠላዉም ሊፈራት ይገባል! የሰው ልጅ በተፈጥሮው ዉስጡ ክፋት ቢኖርበትም ሴቷ በዚህ ረገድ እጂግ የላቀ ክፋትን የተሞላች ነችና…

“የወንዱ ደስታ በራሱ ፍላጎትና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሲሆን የሴቷ ግን የተገላቢጦሽ በእሱ ደስታ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ለዚህም ነው ሴቷ ስታፈቅር ‘አሁን ዓለም ፍጹምና የተዋበች ሆነች’ ትላለች። የሴት ልጅ ነፍስ ጥልቀት በሌለው ኩሬ ዉሃ የምትመስለዉስ ለዚሁ አይደል?

“ዳሩ የወንዱ ነፍስ ደግሞ እጂግ ጥልቅ ናት። የሴት ልጅ በሃይሏ ሙላት የጥልቁን መጨረሻ ለመድረስ ብትሞክር አይቻላትም፤ አልያም እዚያው ሰምጣ ትቀራለች… የብዙዎቹ ሴቶች እጣም ይኸው ነበር።”

አሮጊቷ በጽሞና ስታደምጥ ቆይታ፦ “ዛራቱስትራ ብዙ መልካም ነገርን እነሆ ተናገረ! በተለይም ለወጣቶቹ ሴቶች የሚጠቅማቸዉን እዉነት አደመጥሁለት፤

“ከሁሉ የሚደንቀኝ ዛራቱስትራ ስለሴት ያለው እዉቀት እጂግ ጥቂት ሆኖ ሳለ ስለእነሱ የተናገረው ግን በሙሉ ትክክል መሆኑ ነው። ምናልባት ስህተት ያላገኘሁበት ለሴት የማይቻላት ነገር ባለመኖሩ ይሆን?

“ለማንኛዉም የምታዉቀዉን እንደማታዉቀው ሁን። ጥቂቷ እዉቀትህን አሁንም በሚገባ አፍነህ ያዛት… አለበለዚያ እንዲህ እየጮኸች ታሳጣኻለች” አለችኝ።

“እባክሽ አንች ሴት … የአንችን ትንሽ እዉነት ደግሞ ልትነግሪኝ ትችያለሽ?” በማለት ጠየቅዃት።

አሮጊቷ ድምጻን ዝቅ አድርጋ፦ “ወደሴቶች ትሄዳለህን? እንግዲያዉስ ጅራፍህን ዘንግተህ አትሂድ… በእኔ ዘንድ ያለው እዉነት ይኸው ነው።”

 

ምንጭ፦

ጥበብ መጽሃፍ

ቅጽ 1

9ኛ እትም

ከጲላጦስ

(ኃይለጊዮርጊስ ማሞ)

ገጽ 562 - 565

Author Profile

Avatar

Bin Yam

Member since 4 years ago
    View Profile

    Contact Author

    ወደ ሴቶች ትሄዳለህን? እንግዲያዉስ ጅራፍህን ዘንግተህ አትሂድ 2 reviews

    Write Your Review
    4.5
    2 reviews
    • Gebi

      ምርጥና አስተማሪ ጽሁፍ በህይወታችን ልንተገብረው የሚገባ ሃሳብ ነው። ዛራቱስትራ ምርጥ ፈላስፋ እንደመሆኑ መጠን የሱ የፍልስፍና ዉጤት መሆኑ ደስ ይላል…

    • Bin Yam

      በጥበብ መጽሃፍ ቅጽ 1 9ኛ እትም ከጲላጦስ (ኃይለጊዮርጊስ ማሞ) ክፍል አስራ አንድ ላይ ስለ ዛራስቱስትራ ብዙ አጫችር የፍልስፍና ክፍሎች አንዱ የሆነዉን ክፍል ሳቀርብላችሁ በጣም እንደምትወዱት በማመን ነው። የተሰማችሁን አስተያየት በመስጠት ሃሳባችሁን ግለጹልኝ። መልካም ንባብ!

    Write Your Review

    Your email address will not be published. Required fields are marked *